አዲሷ የጓደኛህ ፍቅረኛና አንተ

አንተና የወንድ ጓደኛህ በጣም ትቀራረባላችሁ። በጣም ትዋደዳላችሁ። ጓደኝነታቹ የጠበቀ ነው። በችግሩ ጊዜ ትደርስለታለህ። እሱም በችግርህ ጊዜ ይደርሳል። ደስታም ሲመጣ አብራችሁ ትካፈላላችሁ። አብራችሁ የግርኳስ ጨዋታ ታያላችሁ። ምሽት ላይ ወደ ባር እየሄዳችሁ ጊዜ ታሳልፋላችሁ። ካሲኖ ትገባላችሁ። ሴቶችን ትለክፋላችሁ። ብቻ በክፉም በደጉም አትነጣጠሉም። ይህ በንዲህ እንዳለ ባጋጣሚ ጓደኛህ አዲስ ፍቅረኛ ይይዛል። ፍቅራቸው እየደራና የምር እየሆነ ይመጣል። ለጓደኛህ የምትመኝለት ነገር በመሆኑ ደስ ይልሃል። እንደድሮው ካንተ ጋር ብዙ ጊዜ ባያሳልፍም ቢያንስ በሳምንት አንዴ ስለምትገናኙ የፍቅረኛው ጣልቃ ገብነት ብዙም አያስከፋህም። ሆኖም ግን አንድ ችግር ይፈጠራል። ግራ በሚያጋባ ሁኔታ አዲሷ ፍቅረኛው ላንተ ያላት አመለካከት አሉታዊ ሆኖ ታገኘዋለህ። ያስከፋሃት ነገር የለም። ብቻ አንተን ባየች ቁጥር ሥራዋ መነጫነጭና ማጉረምረም ነው። በአግባቡም ሰላም አትልህም። ባጭሩ፣ ፊት ትነሳሃለች። ምንም ያደረካት ነገር ስለሌለ በጣም ያበሳጭሃል። እርግጥ ነው የፍቅረኛዋ የቅርብ ጓደኛ ከመሆን በስተቀር ያጠፋኸው አንዳችም በደል የለም። በሷ የተነሳ ጓደኛህን ደግሞ ማጣት የለብህም።

እንደዚህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ የሚከተለውን እርምጃ ውሰድ፦

ችግሯን ለመረዳት ሞክር። የሚያንጨረጭራትንና በጥላቻ ዓይን እንድታይህ የሚያደርጋትን ነገር ለማወቅ ዕቅድ አውጣ። በተጨማሪም ሳታንገራግር ጓደኛህ የሚያውቀው ነገር ካለ “ምን አጥፍቼ ነው?” ብለህ ጠይቀው። የነገረችው ነገር ካለ መቼስ አይደብቅህም። እሱ ምንም እንደማያውቅ ከተረዳህ አሁን የራስህን መፍትሄ አፈላልግ።

የሚከተሉትን እንደ መነሻ ምክንያቶች ውሰድ፦

የሴት ጓደኛ አለመያዝህ

ሴቶች ጥሩና የሚታመን ወንድ ካጋጠማቸው ይህን ወንድ ለሌላ አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም። እናም መሰናክል ሊሆን የሚችል እንቅፋት መንገዳቸው ላይ ከተገኘ እሱን እንደምንም ብሎ ማስወገድ ተቀዳሚ ተግባራቸው ያደርጉታል። ያንተ የሴት ጓደኛ አለመያዝ እሷን በፍቅረኛዋ ላይ ሙሉ እምነት እንዳትጥል ያደርጋታል። ምክንያቱም ከሌላ ሴት ጋር ልታጣብሰው ትችላለህ ብላ ስለምታስብ ነው። ወይም ያንተን ብቸኛ መሆን ሲያይ የድሮ ብቸኝነቱን ይናፍቃል የሚል ስጋት ስለሚያድርባት ነው። ይህ ከሆነ ችግሯ ቀላሉ መፍትሄ ባንተ ላይ እምነት እንዲኖራት ማድረግና ከጓደኛህ ጋር ወደ ባር ስትሄዱ ሴት ፍለጋ አለመሆኑን ማሳመን ነው። ይህንንም ለማሳካት ጓደኛህን ከሌሎች ጓደኞችህ ጋር ሆነህ ስትጠራው እሷንም ጋብዛት። አልፎ አልፎ እየመጣች ከናንተ ጋር ጊዜ ታሳልፍ። ያኔ ፍቅረኛዋ የትና ከነማን ጋር እንደሚውል ስታውቅ ትረጋጋለች። አንተንም “ከጠላቶቿ” ራዳር ውጭ ታደርግሃለች።

እሷን ማግለልህ

ብዙ ሴቶች (በተለይ ዓይናፋር የሆኑት) አዲስ የወንድ ጓደኛ ሲይዙ አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ነገር የፍቅረኛቸውን የወንድ ጓደኞች መተዋወቅና መግባባት ነው። በተለይ ወንድየው ብዙ ጓደኞች ካሉት የነሱን ባህሪ መረዳትና ቀልዶቻቸውን ማጣጣም ለአዲስ መጪዋ ይከብዳል። የምትናገሩትና የምትቀልዱት ስለማይገባት፣ ባይተዋርነት ሊሰማት ይችላል። አንተ ደግሞ የፍቅረኛዋ ቅርብ ጓደኛ እንደመሆንህ መጠን ቤተኝነት እንዲሰማት ምንም ዓይነት ጥረት ካላደረግህ ቂም ልቲዝብህ ትችላለች። ስለዚህ ምንም እንኳ ዘምባባ አንጥፈህ መቀበል ባይጠበቅብህም፣ አዲሷ ቤተኛ ስትመጣ እንደ እንግዳነቷ ጥሩ እንግዳ ተቀባይ ሆነህ ማስተናገድ ይጠበቅብሃል። እናም ተነጥላ ብቻዋን ስትሆንና ባይተዋርነት ሲሰማት ቀርበህ ማጫወትና ግሩፓችሁን እንድትቀላቀል መጋበዝና ማበረታታት ላንተ ያላትን አመለካከት እንድትቀይር ያስገድዳታል።

ምናልባት ባንተና በጓደኛህ መካከል ባለው ጓደኝነት ቀንታ ይሆናል

ሴቶች የፍቅረኛቸውን ሙሉ አትኩሮት መሳብ ይፈልጋሉ። አንተ ያን ሙሉ አትኩሮት እንዳታገኝ ካደረካት ተቀናቃኟ ሆንክ ማለት ነው። ለፍቅረኛዋ የመጀመሪያ ተጠሪ እንጂ ሁለተኛ መሆን አትፈልግም። ፍቅረኛዋ ከባድም ይሁን ቀላል ችግር ሲያጋጥመው ያንተን ምክር ብቻ የሚሰማ ከሆነ፣ ይህ አካሄድ በሷ በኩል ተቀባይነት አይኖረውም። ያንተን ጣልቃ ገብነት እየገነባችው ላለው ግንኙነት ጠር አድርጋ ትወስደዋለች። ስለዚህ የሷም ሐሳብ እንዳንተው ተሰሚነት እንዳለው ልታሳምናት ይገባል። እሱ ያንተን ምክር ሲጠይቅ፣ ምላሽ ከመስጠትህ በፊት፣ እሷ የምትሰጠው ሐሳብ ወይም ምክር ካለ ጠይቃት። አሁን ባለችበት ደረጃ የአንደኛነቱን ቦታ ባታገኝ እንኳ በፍቅረኛዋ ጉዳይ ላይ ካንተ እኩል ተሰሚነት ማግኘቷ ያስደስታታል።

ወዘተ

ይህን ሁሉ ጥረህ ልትቀየር ካልቻለች ወይም ችግሯን ማወቅ ካቃተህ፣ ያለህ አማራጭ ሁኔታውን ዘርዝረህ ለጓደኛህ ከነገርክ በኋላ እንደሷው ሙደኛ መሆን ነው። ስትፈጠርም ነገረኛ ሳትሆን ስለማትቀር በተቻለህ ከሷ ራቅ።

የውዱ ጓደኛህና የፍቅረኛው ግንኙነት የሆነ መንገድ ላይ ሲደርሱ ሊያከትም ስለሚችል፣ በሷ የተነሳ ከጓደኛህ  ጋር ያለህን ግንኙነት አታቋርጥ—ለዓመታት የገነባችሁት ጓደኝነት በአንድ ወር ውስጥ በተገናኛት ልጅ ሰበብ መፍረስ የለበትም። ግንኙነታቸው ከሰመረም አንተ ከሱ ጋር ያለህን ግንኙነት ቀጥልበት። እሷ ደግሞ ምናልባት አንድ ቀን ጥፋተኛ መሆኗን ተገንዝባ ትቀየር ይሆናል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s