“ፍቅረኛዬን ከሌላ ሴት ጋር ያዝኩት”

ሰላም አንባቢዎች! ሊሊ የምትባል አንባቢያችን የሚከተለውን መልዕክት ልካልን ነበር። እኛም ምላሽ አዘጋጅተናል።

ሊሊ የጻፈችልን መልዕክት ባጭሩ፣

“ከፍቅረኛዬ ጋር አብረን ከሆንን አምስት አመት ሆኖናል። ከሁለት አመት ወዲህ ግን ልቤ ጠርጥሮታል። ከአንድ ወር በፊት አንድ ሁለት ቀን ስልክ ስደውልለት አያነሳም። አንድ ቀን መንገድ ላይ ታክሲ ስጠብቅ ከሆነች ሴት ጋር በመኪና ሲያልፍ አየሁት። ከሶስት አመት በፊት ከዚህች ሴት ጋር አይቼው ነበር። እናም ስንገናኝ እውነቱን እንዲነግረኝ ጠየኩት። እሺ ብሎ ነገረኝ። የሚያውቃት ከ12 አመት በፊት እንደነበር ነገረኝ። ወሲብ እንደፈፀሙና ለገንዘብ ብሎ እንደቀረባት ነገር ግን ወሲብ ላይ እንደማትመቸውም ነገረኝ። ባለትዳርና የልጆች እናት ናት። የሚገርመው ዕድሜው ከ46 እስከ 50 ይሆናል። ሥራው መሐንዲስ ሲሆን መኖርያ ቤትም አለው። ስለዚህ ሰው ምን ትመክሩኛላችሁ?”

ውድ ሊሊ፣

በመጀመርያ ስለጻፍሽልን ከልብ እናመሰግናለን። ከፍቅረኛሽ ጋር ያለሽ ግንኙነት ጥሩ ሁኔታ ላይ አለመሆኑን እያዘንን ምክራችን የሚከተለው ይሆናል።

ከፍቅረኛሽ ጋር አምስት አመት ብትኖሩም እንደተረዳነው ከሆነ ጊዜውን ያሳለፋችሁት ብዙም ሳትተዋወቁ ነው። ሰፊ የሆነ የዕድሜም ልዩነት በመሐላቹ ያለም ይመስለናል። ምክንያቱም ዕድሜው ከ46 እስከ 50 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ መሆኑ እንዳስገረመሽ ጽፈሻል። ሌላው የተገነዘብነው ነገር ከእሱ ጋር አብረሽ እንደማትኖሪ ነው። የራሱ ቤትና ሥራ እንዳለው ነገርሽናል።

የኛ መላምት ይህን ይመስላል።

1 – ፍቅረኛዬ ያልሽው ሰው ሌላን ሴት ሳይሆን በአንቺ ላይ የደረበው አንቺን ለ5 አመት በሌላ ሴት ላይ መደረቡን

2 – ያቺንም ሴት ሳያቆም እንደሚያያት

3 – አንቺ የማታውቂያት የትዳር ጓደኛም ልትኖረው ትችላለች። ቤቱ ሄደሽ ታውቂያለሽ? ብቻውን ነው የሚኖረው? ለገንዝብ ብዬ ነው የቀረብኳት ያላት ሴት ሚስቱ ብትሆንስ? እሱን በመጠይቅ ብቻ ሳይሆን በሌላ መንገድ በደንብ ልታረጋግጪ የምትችይበት ሁኔታ አለ?

4 – የዛሬ 12 ዓመት በጥቅም የተዋወቃትን ሴት አሁን ድረስ አንቺን በጎን አስቀምጦ የሚያያት ለምንድነው? እውነት እንደሚለው በወሲብ ስለማታረካው ነበር የራቃት ወይንስ አሁንም ለጥቅሙ ሲል ይፈልጋታል?

5 – ሰውየው አንቺን መተው አይፈልግም። ያቺንም መተው አይፈልግም። ለአምስት አመት ደብቆሽ የኖረውን ጉዳይ አሁን ነግሮሻል። ለምን ይመስልሻል?

6 – አንቺ ከሱ የምታገኝው ጥቅም ምንድነው? በተለይ በዕድሜ ብዙ የምትለያዩ ከሆነና በግልጽ ከሌላ ሴት ጋር ለጥቅም ብሎ እንደሚተኛ እየነገረሽ አብረሽው ለመኖር የምትፈልጊበት ምክንያት ምንድነው? ከሱ የተሻለ ወንድ አላገኝም ብለሽ ነው? ስለምታፈቅሪው ነው? ፍቅር እኮ ታድያ እኩል መሆን አለበት።

7 – አንቺ እንደምታፈቅሪው እሱ ካላፈቀረሽና ካላከበረሽ የፍቅር ትርጉሙ ምንድነው?

8 – አንቺ እሱን የምታይው በፍቅረኛ ዓይን ሲሆን እሱ ግን አንቺን የሚያይሽ በውሽማ ዓይን ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት እንደ ውቅያኖስ የሰፋ ነው።

እንደኛ ዕምነት ከሆነ የሚከተሉትን ብትፈጽሚ ራስሽን ከብዙ ራስምታትና አላስፈላጊ ችግር ውስጥ ነፃ ታወጫለሽ።

1 – ከዚህ ግንኙነት ምንድነው የምትፈልጊው? ራስሽን በደንብ ጠይቂው። የወደፊት ዓላማሽ ምንድነው? ከሱ ጋር ተጋብቶ መኖር?

2 – የእሱስ አላማ ምንድነው? አምስት አመት አብራችሁ አሳለፋችሁ። ከዚህ በኋላ ያለውንስ ጊዜ እንዴት ማሳለፍ ነው የሚፈልገው? ካንቺ ጋር ትዳር መስርቶ የመኖር ዓላማ አለው? ከሆነ ደግሞ መቼ? ቁርጥ ያለ ጊዜና ሰዓት ልታገኚ ይገባል። ዝም ብሎ ተስፋ ብቻ ሳይሆን።

3 – ከሴትዮዋ ጋር አሁን ያለው ግንኙነት ምንድነው? እንዴትስ ልታረጋግጪ ትችያለሽ?

4 – ከሴትዮዋ ጋር ዛሬ ምንም ግንኙነት የለኝም ቢልሽ ምን ማስተማመኛ አለሽ? እሱ ስላለሽ ብቻ እንደሞኝ ልታምኝው ነው?

5 – በዕድሜ ስለሚበልጥሽ እስከዛሬ አታሎሽ ሊሆን ይችላል። ዳግም ላለመታለል ልትወስጂው የምትችይው እርምጃ ምንድነው? አንዴ ያማገጠ ሁሌም አማጋጭ መሆኑን አትዘንጊ።

ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ካገኘሽ በኋላ ውሳኔ ላይ የመድረስ ፋንታ ያንቺ ይሆናል። እኛ ተለያዩ ለማለት ይከብደናል። ነገር ግን ግንኙነታችሁ አሁን ባለበት ሁኔታ ጤናማ አለመሆኑንና መፍትሄ ከሌለው ብትለያዩ ጥሩ ነው የሚል ዕምነት አለን። ላንቺ የሚሆን ወንድ አይጠፋም። በተለይ ወጣት ከሆንሽ፣ ገና ብዙ ጊዜ ስላለሽ፣ አማርጠሽ፣ ኮርተሽ የሚያፈቅርሽንና “ካንቺ ሌላ ሴት ለምኔ?!” የሚል ወንድ ታገኛለሽ። ወጣት ባትሆኚም የሚመጥንሽን አፍቃሪ ወንድ አታጭም። በራስሽ የምትተማመኚ ከሆንሽ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ብትሆኚ የሚንገበገብልሽን ወንድ አታጭም። ካልተገኘም፣ ፍቅረኛዬ የምትይውን ሰው ከሌላ ሴት ጋር ከምትጋሪ፣ መጋራትን እንደ ምርጫ የማታዪ ከሆነ፣ የሚሆንሽ ሰው እስኪገኝ ድረስ ለብቻሽ መኖር የተሻለ አማራጭ ነው። ከዚህ ፍቅረኛሽ ጋር መለያየቱ ሊከብድሽና መጥፎ ሐዘን ውስጥ ሊከትሽ ይችላል። ግን በህይወትሽ ደስተኛ ለመሆን የግድ ወንድ ያስፈልግሻል ማለት አይደለም። በተጨማሪ ደግሞ እዚህም፣ እዚያም እንደውሻ ሲቀላውጥ በወሲብ የሚተላለፍ በሽታ ቢያሸክምሽስ? ራስሽን ልትጠብቂ ይገባል። ከራስ በላይ ንፋስ ነው።

ምርጫው ያንቺ ነው። ተከብረሽ አንቺን ብቻ ከሚመርጥ ሰው ጋር መኖር ወይም ሳትከበሪ ከሌላ ሴት ጋር እያፈራረቀ ከሚበዳሽ ወንድ ጋር መኖር። ነፃነት ወይስ ባርነት?

– ነፂ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s