8

ብትደርብብህስ?

ባለፈው “ቢደርብብሽስ” በሚል ርዕስ፣ ባል ወይም ፍቅረኛ ተደብቆ ተደራቢ የሴት ፍቅረኛ መያዝ አለመያዙን ለማወቅ የሚያስረዱ ምልክቶችን ጽፈን ነበር። በዛሬው ርዕሳችን ደግሞ ሚስት ወይም ፍቅረኛ ተደራቢ የወንድ ፍቅረኛ መያዝ አለመያዟን ፍንጭ የሚሰጡ ምልክቶችን እንዘረዝራለን።

ወንዶች ለትዳራቸው ወይም ለፍቅረኛቸው የማይታመኑ እንደሚሆኑ ሁሉ፤ ሴቶችም ከወንዶች ባልተናነሰ መልኩ ከትዳራቸው ወይም ከፍቅረኛቸው ውጭ ሊማግጡ (ቺት ሊያደርጉ) ይችላሉ። “እሷ ታማኜ ናት፤ ከልቧ ታፈቅረኛለች፤ ሌላ ወንድ በፍጹም አታስብም፤ ሐይማኖተኛና ንጹህ አፍቃሪዬ ናት፤ ህይወቷን አሳልፋ ለእኔ ትሰጣለች!” በማለት፣ በእርግጠኝነት ቀበቶህን አጥብቀህ የምትከራከርላት ሚስትህ ወይም ፍቅረኛህ ከሌላ ወንድ ጋር በድብቅ የፍቅር ግንኙነት ጀምራ ብትይዛት ለማመን ይከብድህ ይሆናል። አንዳንድ ወንዶች ራሳቸውን የሚገድሉት ወይም ፍቅረኛቸውንና አፍቃሪዋን ገድለው እስርቤት ቀሪ ዘመናቸውን የሚያሳልፉትም በዚህ ምክንያት ነው።

ሚስትህ ወይም ፍቅረኛህ በላይህ ላይ ደርባ ከሆነ የሚከተሉት ምልክቶች ፍንጭ ሰጪዎች ናቸው፦

1) ያልተለመደ የባህሪ ለውጥ ካሳየች። ገና ስትተዋወቁ ብዙ የወንድ ጓደኞች ካሏትና ግንኙነት ከጀመራችሁም በኋላ ከነሱ ጋር ጊዜዋን አልፎ አልፎ የምታሳልፍ ከሆነ፣ ይሄ ብዙም ሊያሳስብህ አይገባም። ነገር ግን በቅርቡ ከሆነ ወንድ ጋር ጓደኝነት መጀመሯን ከነገረችህ ወይም ወሬ ከሰማህ፣ መጠርጠር ይኖርብኻል።

2) ያንተን ርዳታ መፈለግ ካቆመች። ከዚህ በፊት አንተ በሌለህበት ጥናት የማታጠና፣ ገበያ ወይም ጂም የማትሄድ፣ መንገድ የማታቋርጥ ከሆነ፤ ሆኖም ከመሬት ተነስታ እነዚህን ነገሮች ብቻዋን ማድረግ ከጀመረች፣ ምክንያቷም ግልጽ ካልሆነ፣ ሌላ ሰው ያንተን ቦታ ተክቶ እየተራዳት መሆን አለበት።

3) መናደድ ካቆመች። ከዚህ በፊት ምሳ አብረኻት ካልበላህ፣ ግንቧሯን ሳትስም ከቤት ከወጣህ፣ ከጓደኞቿ ጋር ለመዝናናት አልወጣም ካልክ፣ ስልክ ሳትደውልላት ከቀረህ በጣም የምትናደድ ከነበረች፤ አሁን ግን ያ ባህሪህ ምንም የማያናድዳት ከሆነ፣ ወይ ላንተ ያላት ፍቅር እየተሟጠጠ መጥቷል አልያም ሌላ ሰው ቦታህን ወስዷል። ያለምክንያት ግዴለሽ ልትሆን አትችልም።

4) በጣም ሚስጥረኛ መሆን ካበዛች። እንደድሮው ስለውሎዋ አታወራም። ገና ምንም ሳትጠይቃት ስታደርግ የዋለችውን ሁሉ ትቀባጥርልህ ነበረች፣ ዛሬ ግን አንተ ነህ ጠያቂ። ጠይቀህም በቂ ምላሽ አታገኝም። የተድበሰበሰ ምላሽ ነው የምትሰጥህ ወይም ከነጭራሹ የማውራት ፍላጎት የላትም። ሚስጥረኛነት ካበዛች፣ አንተ እንድታውቅባት የማትፈልገው ነገር አለ ወይም አንተ ጋር የምትመጣው ከሌላ ሰው ጋር አውርታ ባትሪዋን ከጨረሰች በኋላ ነው።

5) ከመጠን በላይ ጥሩ ከሆነች። ስታጠፋ አትቆጣህም። ስትበድላት ስቃ ታሳልፋለች ወይም ትንሽ አኩርፋ የረሳች መስላ ታልፈዋለች። እስኪሰለችህ ድረስ በስልክም ሆነ አልጋ ላይ በጣም እንደምትወድህ ትነግርኻለች። በቀን አንዴ ወይም ሁለቴ እወድኻለው የምትልህ፣ በቀን ሺ ጊዜ መውደዷን በተለያየ መንገድ የምትገልጽ ከሆነ፣ አንተን ለመካስ የምታደርገው ጥረት ሊሆን ይችላል። ከአንተ ተደብቃ ሌላ ወንድ በመብዳቷ ወይም በመሳሟ ስለተጸጸተች ወይም “ሌላ ፍቅረኛ ይዛለች” ብለህ እንዳትጠረጥራት ከመጠን በላይ ጥሩ ሆና ትገኝ ይሆናል።

በርግጥ እነዚህ ምልክቶች ሚስትህ ወይም ፍቅረኛህ ባንተ ላይ ስለመደረቧ መቶ በመቶ የሚያረጋግጡ አይደሉም። “ከጀርባዬ እያማግጥሽ ነው” የሚል ክስ ከማቅረብህ በፊትና ግንኙነታችሁን አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ ከመወሰንህ በፊት ነገሮችን በደንብ መርምር። በደንብ አጣራ። በስማበለው ወይም መረጃ በሌለው ጥርጣሬ አትደንፋ። ጥርጣሬህ ከቅናት የመነጨ ይሆናል። የማያከራክር መረጃ እጅህ ውስጥ እስኪገባ ድረስ ጥርጣሬህን በውስጥህ ያዝ። ሰው ነገረኝ ብለህ ወይም ከሌላ ወንድ ጋር ስታወራ፣ ጊዜ ስታሳልፍ ስላየኻት ብቻ በአማጋጭነት መኮነን የለብህም።

“እያማገጠችብኝ ነው” ብለህ የምታስብ ከሆነ፣ ስለማማገጥ ሳታነሳ በግልጽ አወያያት። ችግር ካለ ጠይቃት። ባህሪዋ ሰሞኑን እየተቀያየረብህ መምጣቱን ምሳሌ እየጠቀስክ ንገራት። የሚያስጨንቃት ነገር ካለ ማወቅ እንደምትፈልግና መፍትሄ በማፈላለግ እንደምትተባበራት ግለጽላት። ፍላጎትህ ነገሮችን ካንተ እንድትደብቅ ሳይሆን ግልጽ ሆና የሚያስጨንቃትን ነገር እንድታወያይህ መሆን አለበት። በደንብ መነጋገር መቻል አለባችሁ። ውይይት የጎደለው ግንኙነት ስኬታማ ሊሆን አይችልም። ያንተ አቀራረብ ወሳኝነት አለው። አቀራረብህ ካላስፈራት ወይም ወደ ኋላ እንድታፈገፍግ ካላደረጋት፣ ቀስ በቀስ የሚያሳስባትን ነገር ወይም ባህሪዋ የተለወጠበትን ምክንያት ትነግርኻለች።

መቶ በመቶ እርግጠኛ ካልሆንክ፣ የሆንክ ቢመስልህ እንኳ “እያደረግሽ ያለውን ደርሼበታለሁ! በጀርባዬ ምን እያደረግሽ እንደሆነ አውቃለሁ!” በማለት ውንጀላ ውስጥ አትግባ። ውንጀላህ እውነት ሆኖ ካልተገኘ፣ ልታምናት ባለመቻልህና ባላደረገችው ነገር በመወንጀልህ አዝና ልትለይህ ትችላለች። ባንተ ላይ መደረቧን ብታውቅ እንኳ ከሷ እስኪመጣ ድረስ የማታውቅ መስለህ ጠብቅ። ምንም ከሷ የሚመጣ ነገር ከሌላ የማያከራክር መረጃ በእጅህ ከያዝክ በኋላ አፋጥጣት። መለያየት የግድ ከሆነ ደግሞ በሰላም አሰናብታት። “ልግደልሽ፣ ልስቀልሽ፣ ልሰንጥቅሽ፣ ራሴን ልግደል፣ ወ.ዘ.ተ.” ድሮ የቀረ ነገር ነው። በሆነ ሰዓት ትወድህ ነበር፣ አሁን አትወድህም። አከተመ። በኃይል ያንተ ልታደርጋት አትችልም። “የእኔ ካልሆንሽ አፈር ይብላሽ!” ማለት ደግሞ ራስ ወዳድነት ነው። ከልብህ የምታፈቅራት ከሆነ ምኞትህ እሷን ደስተኛ ማድረግ ነው። “መንገዱን ጨርቅ ያድርግልሽ” ብለህ ሸኛት። ነገር ግን ምኞትህ እሷን መበቀል ከሆነ የምትወደው እሷን ሳይሆን ራስህን ነው።

3

ቢደርብብሽስ?

ከሶስት ወንዶች መካከል አንደኛው በድብቅ ተደራቢ ፍቅረኛ እንደሚይዝ ጥናቶች ያሳያሉ። “ታማኜ ነው፤ ከልቡ ያፈቅረኛል፤ ሌላ ሴት በፍጹም አያስብም!” በማለት እርግጠኛ ሆነሽ የምትመሰክሪለት ባልሽ ወይም ፍቅረኛሽ፣ ከሌላ ሴት ጋር በድብቅ የፍቅር ግንኙነት ጀምሮ ብትይዥው ለማመን ይከብድሽ ይሆናል።

ፍቅረኛሽ ወይም ባለቤትሽ፣ በላይሽ ላይ ሌላ ሴት መደረብ፣ አለመደረቡን ለማወቅ ከፈለግሽ፦

1) ልብሽን በጥሞና አዳምጪ። ልብሽ የሆነ ነገር መጠርጠር ከጀመረና ሁል ጊዜ የባልሽን ወይም የፍቅረኛሽ የገንዘብ ቦርሳ ወይም ኪሱን ፈትሺ፣ ፈትሺ የሚልሽ ከሆነ፤ ሞባይሉን እንድታዪና ኢሜይሉን እንድታነቢ ከገፋፋሽ፤ ባልሽ ወይም ፍቅረኛሽ የሆነ ነገር ከአንቺ እየደበቀ መሆን አለበት፤ በሁለታችሁ መካከል ችግር ተፈጥሯል ማለት ነው። ምንም ነገር ካላገኘሽበት፣ ቅሬታሽን በመግለጽ የደበቀሽ ነገር ካለ ግልጽ ሆኖ እንዲነግርሽ አዋይው። በርግጥ ዝም ብሎ መጠራጠር ጥሩ አይደለም። ምክንያታዊ ካልሆነ ቅናት የመነጨ ሊሆን ይችላል። ምክንያታዊ ያልሆነ ቅናት ደግሞ የመልካም ግንኙነት ፀር ነው። ነገር ግን ጥርጣሬሽ ምክንያታዊ ከሆነ፣ ለጥርጣሬሽ መፍትሄ እስክታገኚ ድረስ ፍንጭ ፍለጋሽን አታቋርጭ። አንዳንዴ ደግሞ ምን ያህል እንደምትወጂው ለማወቅ ሲል፣ አውቆ እንድትጠረጥሪው ሊያደርግሽ ይችላል፤ ወደ ቅናት ዓለም፣ ወደ ጥርጣሬ ይገፋፋሽ ይሆናል። አንዱን ከሌላኛው ለይቶ ማወቅ ያንቺ ፋንታ ነው።

2) ያለባሕሪው ቁጡነት ካበዛ ችግር አለ ማለት ነው። በሰላም ስታናግሪውም ሆነ ስለግንኙነታችሁ ስታዋይው ዓይኖችሽን እያየ የማያዋራሽ ከሆነ፣ አንድ የቋጠረው ሚስጢር መኖር አለበት።

3) ጥያቄ ስታበዢበት አንድ ፍንጭ ከሰጠሽ ፍንጩን ችላ አትበይ። ለምሳሌ እየደጋገመች የምትደውልለት ሴት ካለችና የሥራ ቦታ ባልደረባው መሆኗን ገልጾ ዝም ካለ፣ ከባልደረባነቷ በላይ ሌላም ነገር ስለሚኖር በመሐከላቸው ያለውን ግንኙነት በደንብ አጣርተሽ እወቂ።

4) በጣም የሚቀርባት የሴት ጓደኛ ካለችው እሷን በዓይነ ቁራኛ ተከታተያት። በርግጥ ለምን የሴት ጓደኛ ያዝክ ወይም ኖረህ ማለት አትችይም። አንቺም የወንድ ጓደኞች ሊኖሩሽ ስለሚችሉ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ጓደኝነት ሲጠብቅ ወደ ፍቅር ሊያመራ ይችላል። ከአንቺ ይልቅ ከሴት ጓደኛው ጋር ብዙ ጊዜ የሚያሳልፍ ከሆነ ደስተኛ እንዳልሆንሽ ንገሪው። የማይሰማሽ ከሆነ ነገር አለ ማለት ነው።

5) አንዴ ካታለለሽ ወይም ከዋሸሽ አሳፍሪው። ደግሞ ካታለለሽ ወይም ከዋሸሽ ግን በራስሽ እፈሪ። ለምሳሌ ሳይበር ላይ ከተዋወቃት ልጅ ጋር ሲያወራ ይዘሽው ስለሷ ከዋሸሽ፣ ደግሞ እስኪዋሽሽ አትጠብቂ። “ወይ እሷን፣ ወይ እኔን ምረጥ” በይው! በአካል ባያገኛትም በሐሳቡ ከእሷ ጋር ስለሆነ በአንቺ ላይ እንደ ደረባት ወይም በሐሳቡ እንደ ወሸማት ቁጠሪ።

6) “ችግሩ ከእኔ ይሆናል” እያልሽ፣ ራስሽን እየወቀሽ፣ እሱ ከሌላ ሴት ጋር ዓለሙን ሲቀጭ፣ አንቺ በሐዘን አትቆዝሚ። የልብሽን ጥርጣሬ አዳምጪው። ልብሽ አንዴ ሊዋሽሽ ይችላል፣ ደግሞ ግን አይዋሽሽም። እየተጠራጠርሽ አብሮ ከመኖር፣ ከጥርጣሬ ነጻ ሆነሽ መኖር ጤናማነት ነው። ሌላ ሴት እያየ ከሆነ በግልጽ እንዲነግርሽ ጠይቂው። ይነጫነጭ፣ ያኩርፍ። እውነትን የማወቅ መብት አለሽ።

7) ለመናገር ፈቃደኛ ካልሆነ ወይም ሌላ ሴት እንደማያውቅ ከተናገረ፣ ነገር ሳይወሳሰብ ለጥርጣሬሽ መፍትሄ አግኚ። በሚስጢር የሚያደርገውን ነገር ተከታትለሽ አሳማኝ መረጃ በእጅሽ ውስጥ ካስገባሽ በኋላ ለስንብት ራስሽን አዘጋጅ።

8)መለያየትን እንደ አማራጭ ካላየሽ ደግሞ ለምን ሌላ መደረብ እንዳስፈለገው በግልጽ እንዲነግርሽ ጠይቂው። “ከእኔ ምን ጎድሎብህ ነው? በወሲብ ሳትረካ ቀርተህ ነው? እንደ ድሮው ውብ ሆኜ አልታየሁህም?” በማለት አፋጥጪው። ምላሽ ካለው፣ ተወያይታችሁ ችግራችሁን አርሙ። ምላሽ ከሌለው፣ ካንቺ ምንም ነገር ካልጎደለ፣ ጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የእሱ ሆኖ ከተገኘ ግን “ሁለተኛ አይለመደውም” ብለሽ ራስሽን አታታልይ። አንዴ ተደብቆ ፍቅረኛ ከያዘ፣ ነገር ከተረጋጋ በኋላ ተመልሶ ወደ ድሮ ባህሪው መመለስ አያቅተውም። ስለዚህ በውሳኔሽ ላይ በደንብ አስቢበት። በላይሽ ላይ እንደሚደርብ እያወቅሽ፣ አንገትሽን ደፍተሽ መኖር ይሻላል ወይንስ የራስሽን ነጻ ህይወት መምራት? ሆኖም መደረቡ ሰላም ካልነሳሽ፣ የሚመችሽ ከሆነ፣ “ይድላሽ” ባዮች ነን።

3

በአንድ መጽናት አቃተኝ

የአንባቢ ጥያቄ፦ የዕድል ነገር ሆኖ አብዛኛውን ጊዜ የምፈልጋቸውን ሴቶች አገኛለሁ። ነገር ግን አንዴ ተዋውቄ ከበዳኋቸው በኋላ ጠንካራ ግንኙነት መመስረት አልችልም። እንደገና ሌላ ፍለጋ እሄዳለሁ። ችግሬ ምንድነው?

የኛ ምላሽ፦ የችግርህ መንስዔ ሊሆኑ ይችላሉ ያልናቸውን ምክንያቶች እንደሚከተለው ዘርዝረናል፦

1) በአንድ ሴት ፀንቶ መገኘት ያስፈራህ ይሆናል።

2) ያየኻት ሴት ሁሉ ታምርኻለች።

3) ሴቶችን እንደ ካልሲ መቀያየር ያኮራኻል ወይም ያስደስትኻል። ያላቅምህ የምትንጠራራ፣ ጉረኛ ነህ።

4) ከመጠን በላይ ራስህን ትወዳለህ (ናርሲሲት ነህ)።

5) የምትገናኛቸውን ሴቶች በባሕሪ፣ በገንዘብ፣ በትምህርት ደረጃ ወይም በሌሎች መለኪያዎች አትመጥናቸውም ወይም አይመጥኑህም።

6) ሴትን የምትፈልጋት ለስሜት ማስታገሻነት ብቻ ነው።

7) ከአንዳቸውም ሴቶች ፍቅር ይዞህ አያውቅም።

8)ፍቅር ይዞህ ከነበረም፣ ያፈቀርካት ልጅ ስላላፈቀረችህ ወይም ትታህ ሌላ ወንድ ስለያዘች፣ ለሷ ያለህ ስሜት ገና አልበረደልህም። ስለዚህ እሷን ለመርሳት ወይም ለመበቀል ካገኘኻት ሴት ጋር ትወጣለህ።

9) ዘላቂ የፍቅር ጓደኛ ወይም ትዳር የምትፈልግበት ዕድሜ ላይ አይደለህም።

10) በሁሉም ነገር የምትስማማህን ሴት ስታገኝ እንዴት አድርገህ መያዝ እንዳለብህ አታውቅም።

ወ.ዘ.ተ.

ከነዚህ 10 ምክንያቶች ውስጥ ቢያንስ አንዱ አንተን የሚገልጽህ ከሆነ፣ ያን ባሕሪህን ወይም አቋምህን ልትለውጠው ወይም ልታሻሽለው ይገባል። ዘላቂ የሆነ ግንኙነት ዝም ብለህ በቀላሉ የምትጀምረውና የምትጨርሰው ነገር አይደለም። ፍሬያማ ግንኙነት ለመመስረት ጊዜህንና ጉልበትህን ማፍሰስ አለብህ። ጥሩ አፍቃሪና ታማኝ ሆኖ መገኘትም የግድ ነው። ግንኙነትን ግንኙነት የሚያደርገው ወሲብ ብቻ አይደለም። ፍቅር መኖር አለበት። የፋይናንስ አቅምም ወሳኝነት አለው።

“ከግንኙነት የምፈልገው ምንድነው?” ብለህ ራስህንም ጠይቅ። “ወሲብ ብቻ ነው ወይስ ከወሲብ በላይ የምፈልገው ነገር አለ? የምፈልገውን ነገር ማግኘት እችላለሁ? መስጠትስ እችላለሁ?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ካገኘህ፣ ስኬታማ ግንኙነት መመስረት ትችላለህ።